Back

በሻሸመኔ ከተማ የፌዴራልና የክልል የአስተዳደርና የጸጥታ ዘርፍ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ

የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስትር ክቡር አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን ከመጋቢት 9 - 10/2008 ዓ.ም በሻሸመኔ ከተማ ተካሂዶ በነበረው የፌዴራልና የክልል የአስተዳደርና ጸጥታ ዘርፍ ሃላፊዎች ጋር ባደረጉት ውይይትና በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ግጭቶችን በዘላቂነት ለመፍታት ሊደረጉ በሚገባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የሰጡት ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ጥያቄ:- በሻሸመኔ ከተማ የፌዴራልና የክልል የአስተዳደርና የጸጥታ ዘርፍ አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ አላማ  በዋናነት ምን እንደሆነ ቢገልጹልን?


አቶ ካሳ:- የምክክር መድረኩ ዋና አላማ አንደኛ መደበኛ ስራዎች የ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የመጀመሪያ ዓመት ያለፉትን ወራት የስራ አፈጻጸም መገምገም፣ እያንዳንዱ ክልል በአገር ደረጃ እንዲሰሩ የተቀመጡ እቅዶች እንዴት እንደተፈጸሙና እንደተከናወኑ ለማየት ነው። የተቋማዊ አቅም ግንባታ ላይ፣ በወንጀል መከላከል፣ በወንጀል ምርመራ፣ በግጭት አፈታት፣ በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና በህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንዲሁም የኮንትሮባንድ ስራዎች ላይ ባለፉት ወራት እንዴት ነው የተፈጸሙት የሚለው የሚታይ ይሆናል። በዚህ ግምገማ አማካኝነት አንዱ ክልል ከሌላው ክልል ልምድ እንዲለዋወጥና ተሞክሮ እንዲያገኝ በሚያደርግ መንገድ ስራውን መገምገም ነው።

ሁለተኛው በአገር ደረጃ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ተከስተው የነበሩ ሁከቶች እንደነበሩ ይታወቃል። እነዚህን ብጥብጦችና ሁከቶች ለመፍታት የጸጥታ አካላት ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው ይታወቃል። ከእነዚህ ውስጥ የጸጥታ አካላት የነበራቸውን አስተዋጽኦና ችግሩን ለመፍታት ያደረጉትን እንቅስቃሴ በተለይ ከህብረተሰቡ እንዴት ተቀናጅተውና ተባብረው እንደሰሩ ይገመገማል።ከዚህ በመነሳት በቀሪዎቹ ወራቶች ምንድን ነው የምንሰራው?  ትኩረታችን ምንድነው? የሚለው የሚታይ ይሆናል።  

ጥያቄ:-  ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት አስቀድሞ በመከላከል ረገድ የፌዴራል መንግስት በተለይም ተቋሙ ምን እያደረገ ነው?  ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ግጭቶችን ቀድሞ የመከላከል ፖሊሲን ከማስፈጸም አንጻር  እንዴት ነው ከክልሎች ጋር በመሆን ተግባራዊ እያደረገ ያለው?

አቶ ካሳ:- የግጭት መከላከል ስትራቴጂው ላይ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስርዓት አለው። በተለይም ችግሮቹ የሚታወቁባቸው ቀድመው የተጠኑ አካባቢዎች አሉ፡፡በእነዚህ አካባቢዎች በየቀኑ ያለውን ሁኔታ የሚከታተሉ የህዝብ አደረጃጀቶች አሉ። በቀበሌ ያሉ የመንግስት አደረጃጀቶችም ምላሽ እንዲሰጡ ተደርጎ የተጀመሩ ስራዎች አሉ። ይህን የማጠናከር ስራ አንዱ የተቋሙ ቤት ስራ ነው። ሁለተኛ በአስተዳደር ወሰን በአንድ አገር ውስጥ ያሉ ክልሎች ስለሆኑ በሁለት አገር ያለ የድንበር ጥያቄ አይደለም፤ በሁለት ክልሎች መካከል ያለ የድንበር ጥያቄ ነው።የትኛው ጎጥ ከየትኛው ጋር ተካቶ ይተዳደራል? የትኛው ቀበሌ ከየትኛው ጋር የሚለው አሁን በአብዛኛው በአገሪቱ ውስጥ የተጠናቀቀ ሆኖ ያላለቁ አካባቢዎች አሉ። እነዚህን ጥናቶች ተጠንተው አንዳንዶቹን ከክልሎች ጋር በመገናኘት ውሳኔ እንዲያገኙ ተደርጓል። ለምሳሌ በጋምቤላ ዲማና ቤሮ የሚባለው አካባቢ ተፈትቷል፣ በአፋርና በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መካከል የነበረውም ተፈትቶ በጣም ትንንሽ ነገሮች ናቸው የቀሩት። በኦሮሚያና በሶማሌ ክልልም በአብዛኛው አልቆ አሁን አመራሮቹ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በቤንሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ያለውም ተጠናቆ የህዝብ ኮንፈረስ አድርጎ የማጠናቀቅ ስራ እየተሰራ ነው። እነዚህ የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር በግጭት መከላከል ክፍሉ አማካኝነት በቅርብ የሚሰራበት ሁኔታ ነው ያለው።  
 
ከሁሉ በላይ ግን ግጭት ከተፈጠሩ በኋላ የማስተዳደሩ ጉዳይ ሳይሆን ቀድሞ የመከላከሉ ጉዳይ በጣም አስፈላጊ ነው። ስለዚህ ግጭት ሊያስነሱ የሚችሉ ሁኔታዎችን እያጠናን አስቀድሞ ችግር ሳይደርስ የመከላከል ስራዎች ይሰራሉ። በዚህ ረገድ ጥሩ ሙከራዎች አሉ፣ ግን ደግሞ ወደፊት ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት ጉዳይ ነው።ከጎረቤቶቻችን ጋርም በጎሳ፣በብሄር የምንገናኝባቸው አካባቢዎች አሉ። ስለዚህ ኮንትሮባንድ፣ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ጋር በተያያዘ ሊነሱ የሚችሉ ሁኔታዎች አሉ፤ ስለዚህ እነዚህን በአግባቡ እያጠኑ በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ነገሮችን መስራት ያስፈልጋል።  


Pages: 1  2  3