የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም በሃገሪቱ ልማትና ዕድገት ያለው ድርሻ

የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም መንግሥት ልማትን ለማሳለጥ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ካስቀመጣቸው ፕሮግረሞች ውስጥ የሚጠቀስ ነው፡፡ ተበታትኖ ይኖር  የነበረዉን ማህበረሰብ በመንደር በማሰባሰብ የተፈጥሮ ጸጋዎችን ማዕከል በማድረግ ሁለንተናዊ ልማት ለማስገኘት የሚያስችል ልዩ የልማት ፕሮግራም ነዉ፡፡ በመንደር የማሰባሰብ ፕሮግራም ህዝቦች ተበታትነውና ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ በሚኖሩባቸው በሶማሌ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ጋምቤላ ክልሎች ተግባራዊ እየተደረገ ያለ የልማት ፕሮግራም ሲሆን ሥራው ከተጀመረበት ጊዜ (2003 ዓ.ም) አንስቶ እስካሁን የተመዘገበው ውጤት አጅግ አበራታች መሆኑን የፌዴራልና አርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር የዘርፉ ሪፖርት ያመለክታል፡፡

የመንደር ማሰባሰብ ዋና ዓላማው ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች በሕዝብ ሙሉ ተሳትፎ የተሰብሳቢ አባወራዎችና እማወራዎች ፈቃደኝነትን በማረጋገጥ  የንፁህ መጠጥ ውሃ እና ለእንስሳት ግጦሽና ለእርሻ ሥራ የሚሆን በቂ የከርሰ ምድርና የገፀ ምድር ውሃ ተደራሽ በማድረግ እና ለአገልግሎቶች ዝግጁ በማድርግ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚ ልማት ተቋማትና አገልግሎት በማሳደግ፣ የግብርና ግብዓትን በወቅቱና በሚፈለገው መጠን ማቅረብና ከገበያ ጋር የሚኖራቸውን ትስስር በማረጋገጥ የህብረተሰቡ የኑሮ ዘይቤ የሚለወጥበት ሂደት  ነው፡፡

የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነት

በነዚህ የልዩ ድጋፍ ክልሎች የሚኖሩት የህብረተሰብ ክፍሎች ኢኮኖሚያዊ መሠረት እንሰሳትን በማርባት ላይ ብቻ ያተኮረ ከመሆኑ የተነሳ ከቦታ ወደ ቦታ በመዘዋወር ስለሚኖሩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶችን ተጠቃሚ ሳይሆኑ ይኖሩ የነበሩ ናቸው፡፡ በትምህርት፣ በጤና፣ በዘመናዊ የእንሰሳት እርባታ ቴክኖሎጂና በሌሎችም የልማት መስኮች እጅግ ወደ ኋላ የቀሩ በመሆናቸዉ ለከፋ ድህነትና ረሀብ ተጋልጠው የነበሩ ማህብረተሰቦች ናቸው፡፡ ለዚህም ነው መንግስት በነዚህ የሃገራችን አከባቢዎች የሚኖሩትን ህዝቦች ከሃገሪቱ አማካይ ዕድገት ፍትሃዊ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ያለው፤ ለዚህም ማሳያ አንዱና ዋነኛ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ እንዚህን ለዘመናት አስታዋሽ አጥተው የኖሩትን ህዝቦች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የመንደር ማሰባሰብ ሥራ ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም በርግጥም የህብረተሰቡን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ያለ ተግባር ነው፡፡

በመስኖ የማልማት እንቅስቃሴዎች - አፋር

ባሳለፍነው ዓመት በሃገራችን አንዳንድ አከባቢዎች በተለይም በአፋርና የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልሎች የተከሰተው ድርቅ ለመቆጣጠር የሚከብድና በከፍተኛ ደረጃ አቅምን የሚፈታተን የነበረ ቢሆንም ከዚሁ ፕሮግራም ጋር በተያያዘ ላለፉት አምስት ዓመታት በክልሎቹ የተሰሩ ሥራዎች ድርቁን ለመቆጣጠር ትልቅ አቅም ፈጥረዋል፡፡ የመንደር ማሰባሰብ ፕሮግራም ተግባራዊ መደረጉ በዚህ ሂደት የነበረው አስተዋጽዖ በምንም ዓይነት መልኩ የሚናቅ አይደለም፡፡

በእነዚህ  ማህበረሰቦች አካባቢ እንደ ነባራዊ ሁኔታዎቻቸው የተፈጥሮ ፀጋን መሠረት በማድረግ በመንደር በማሰባሰብ  የተፋስስ ውኃና ዝናብ ጠገብ ቦታዎችን የልማት ማዕከል ያደረገ የመንደር ማሰባሰብ ኘሮግራም ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ ሁለንተናዊ ልማት ለማስገኘት አመቺ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡ አበረታች ውጤትም ተገኝቶበታል፡፡

የመንደር የማሰባሰብ ኘሮግራም ምንም እንኳን የ2008 ዓ.ም አፈጻፀሙ በዕቅዱ መሠረት የሚጠበቀውን ያህል ተግባራዊ ባይሆንም በእስካሁን አፈጻፀሙ አበረታች ውጤት ማየት የተቻለበት ነው፡፡ ስኬታማ ማድረግ የሚቻለው መነሻው በየክልሎቹ ያሉትን ነባራዊ ሁኔታዎች ከተፈጥሮ ፀጋዎቻቸው ጋር በማዋሃድ መልከዓ ምድራዊና የተከማቸ የተፈጥሮ ፀጋ ወይም ሀብትና ምቹ ሁኔታዎችን መሠረት ባደረገ መልኩ ቁርጠኛ አመራር በመፍጠርና ህዝባዊ ተሳትፎ በማሳደግ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የተቻለ እንደሆነ ነው፡፡

የንፁህ ውሃ አቅርቦት - ጋምቤላ

መንግሥት የክልሎቹን ህዝባዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያደርጋቸው ጉዞ ቀላል የማይባሉ ማነቆዎች ያሉት ሲሆን የአንዳንድ አፍራሽ ኃይሎች፣ ግለሰቦችና ቡድኖች የሚፈጥሯቸው ያልተገባ ጥቅም ፍለጋ በመንግሥት ጥረት በሰላማዊ መንገድ እየተፈታ ልማቱ እየተፋጠነ መሆኑን ተጠቃሚው ህብረተሰብ በራሱ አንደበት እየተናገረ ይገኛል፡፡

የመንደር  መሰባሰብ  ፕሮግራም ሂደት የሕብረተሰቡን ሕይወት  ለመለወጥ የሕብረተሰቡ ፍላጎትና ተነሳሽነት መሰረት  በመሆኑ  በአራቱ የልዩ ድጋፍ ክልሎች ፕሮግራሙ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት 2003 እስከ 2008 ዓ.ም በ568 የልማት ማዕከላት 342,576 አባወራዎችና እማወራዎችን በመንደር ማሰባሰብ ማእቀፍ ውስጥ ማካተት ተችሏል፡፡

በአራቱ ክልሎች በመንደር የተሰባሰቡ ቤተሰቦች የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመሰረታዊ ጤና አገልግሎትና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በዚህም የአብዛኞቹ ክልሎች የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመሰረታዊ ጤናና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ሽፋን ከአገራዊ አማካይ ጋር ተቀራራቢ ሊሆን ችሏል፡፡ ቀጣዩ የክልሎቹ ዋነኛ ትኩረት ግብዓት በማሟላት በአገልግሎቶቹ ጥራት ላይ የሚያተኩር እንደሚሆን ከዕቅዶች ላይ መመልከት ይቻላል፡፡

የጤና ተቋማትና አገልግሎቶች - ቤንሻንጉል ጉሙዝ

በመንደር የተሰባሰበው ማህበረሰብ በልማት እያደረገ ያለውን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን ከማሳካት ጎን ለጎን መብቱን የሚጠይቅና ግዴታውን የሚወጣ፣ ለመልካም አስተዳደርና ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ ማድረግ ጀምሯል፡፡ ህዝቡም ከልማት ተጠቃሚነት ባሻገር በየደረጃው ያለው አመራርም በብቃትና ክህሎቱ እንዲሻሻል የሚያግዙ የአቅም ማጎልበቻ ድጋፎች ስለሚደረግላቸው ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ ናቸው፡፡

የእንስሳት ውሃ ተቋማት ተደራሽነት - የኢትዮጵያ ሱማሌ ከልል

በክልሎቹ አካባቢ ከዚህ ቀደም ይታይ የነበረው አለመረጋጋትና ግጭቶች ቀንሰው ህብረተሰቡ ትኩረቱን ወደ ልማት አደርጓል፡፡ በአጠቃላይ አራቱ የልዩ ድጋፍ ክልሎች ትላልቅ የመንግስት ኢንቨስትመንቶች፣ የግል ኩባኒያዎችና የቱሪዝም መዳረሻዎች መሆን የቻሉበት ነባራዊ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በነዚህ ክልሎች የሚኖሩ ህዝቦች ልማት ሲረጋገጥ ለሃገራችን ሰላም፣ ልማትና ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ስለሚያበረክት ለኢኮኖሚ ዕድገታችን ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል፡፡